መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 40

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1"አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ" ይላል አምላካችሁ።
2ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፣ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፣ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ።
3የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ቃል፣ "የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ አዘጋጁ፤ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካክሉ።"
4ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፣ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፣ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤
5የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፣ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፣ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
6አንድ ድምጽ፣ "ጩኽ" ይላል፣ "ምን ብዬ ልጩኽ?" አልሁ። "ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው።
7የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው።
8ሣሩ ይደርቃል፣ አበባውም ይረግፋል፣ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።"
9የምስራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፣ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ፣ የምስራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፣ አንሺ፣ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች፣ "እነሆ፣ አምላካችሁ!" ብለሽ ንገሪ።
10ተመልከቱ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል። ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፣ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው።
11መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።
12ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፣ ሰማይንም በስንዝር የለካ፣ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው?
13የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፣ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው?
14ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?
15ተመልከቱ፣ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፣ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል፤ ተመልከቱ፣ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል።
16ሊባኖስ ለማንደጃ፣ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም።
17አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ ከምናምን እንደሚያንሱ፣ እንደ ከንቱ ነገርም ይቈጥራቸዋል።
18እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ?
19የተቀረጸውንስ ምስል! ሠራተኛ ሠርቶታል፤ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፣ የብሩንም ሰንሠለት አፍስሶለታል።
20ለዚህ መባዕ ገንዘቡ ያልበቃው ድሀ የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል።
21አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?
22እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፣ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥
23አለቆችንም እንዳልነበሩ፣ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያሳንሳቸው እርሱ ነው።
24ተመልከቱ፣ ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፣ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፣ እነርሱም ደረቁ፣ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው።
25"እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?" ይላል ቅዱሱ።
26ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።
27ያዕቆብ ሆይ፣ እስራኤልም ሆይ፣ "መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፣ ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች" ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ?
28አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፣ አይታክትም፣ ማስተዋሉም ወሰን የለውም።
29ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፤ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።
30ብላቴኖች ይደክማሉ፣ ይታክቱማል፣ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤
31እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።