መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 38

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ድረስ ታመመ። ስለዚህ፣ ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፣ "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል' አለው።
2ከዚያም፣ ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፣
3"አቤቱ፣ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ።" ሕዝቅያስም እየጮኸ አለቀሰ።
4ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
5"ሂድ፣ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፣ 'የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ እንባህንም አይቻለሁ። ተመልከት፣ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት አጨምራለሁ።
6አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፣ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ።
7እግዚአብሔርም የተገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል፦
8ተመልከት፣ በአካዝ የጥላ ስፍረ-ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋር የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።" ስለዚህ ፀሐይም በጥላ ስፍረ-ሰዓት ላይ የወረደበት ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።
9የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምሞ ከደዌው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሕፈት ይህ ነው፦
10"እኔ፣ በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲኦል በሮች እገባለሁ፤ የቀረው ዘመኔ ጐደለብኝ አልሁ።
11ደግሞም፣ በሕያዋን ምድር እግዚአብሔርን አላይም፤ በዓለምም ከሚኖሩ ጋር ሰውን እንግዲህ አልመለከትም አልሁ።
12ማደሪያዬ ተነቀለች፣ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፤ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከማለዳም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ።
13እስኪነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ።
14እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፣ እንደ ርግብም አጕረመረምሁ፤ ዓይኖቼ ወደ ላይ ከማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፣ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ።
15ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፣ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ።
16ጌታ ሆይ፣ የላክኸው መከራ ለእኔ መልካም ነው፤ ሕይወቴ ተመልሶ ይሰጠኝ፤ አንተም ፈወስኸኝ ወደ ሕይወትም መለስኸኝ።
17ታላቅ ምሬት ለጥቅሜ ሆነ። አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጕድጓድ አዳንሃት፤ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጥለሃልና።
18ሲኦል አያመሰግንህምና፤ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጕድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም።
19እኔ ዛሬ አንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆች እውነትህን ያስታውቃል።
20እግዚአብሔር ያድነኛል፣ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው ዕቃ እንዘምራለን።"
21አሁን ኢሳይያስም፣ "የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት፣ እርሱም ይፈወሳል" ብሎ ነበር።
22ሕዝቅያስም፣ "ወደ እግዚአብሔር ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድር ነው?" ብሎ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።