መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 26

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያም ቀን ይህ ቅኔ በይሁዳ ምድር ላይ ይዘመራል። የጸናች ከተማ አለችን፤ ለቅጥርና ለምሽግ መድኃኒትን አድርጎባታል።
2እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ።
3በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትጸና አእምሮ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
4ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም ዐለት ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ።
5በኩራት የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ የተመሸገችውን ከተማ ወደ ምድር ያዋርዳል፤ እስከ መሬት ድረስ ያወርዳታል፤ እስከ አፈርም ድረስ ያርዳታል።
6በድሆች እንዲሁም በችግረኞች ረገጣ የምትረገጥ ትሆናለች።
7የጻድቃን መንገድ ደልዳላ ናት፣ አንተ ጻድቅ የሆንህ የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ።
8አዎን፣ በፍርድህ መንገድ ጠብቀንሃል፤ ስምህም መታሰቢያህም ምኞታችን ነው።
9ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች። ፍርድህ ወደምድር በመጣ ጊዜ በዓለም የሚኖሩት ጽድቅን ይማራሉና።
10ለኃጢአተኛ ሞገስ ይደረግለት፣ ነገር ግን ጽድቅን አይማርም። በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋል፤ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያይም።
11እግዚአብሔር ሆይ፣ እጅህ ከፍ ብላ ተነሣች፣ ነገር ግን አላስተዋሉም። ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ ምክንያቱም እሳትም ጠላቶችህን ትበላቸዋለች።
12እግዚአብሔር ሆይ፣ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ።
13አቤቱ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፣ ከአንተ በተጨማሪ ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤ ነገር ግን የአንተን ስም ብቻ እናስባለን።
14እነርሱ ሞተዋል፣ በሕይወት አይኖሩም፤ ሞተዋል፣ አይነሡም፤ በእርግጥ፣ አንተ በፍርድ መጥተህ አጥፍተሃቸዋል፣ መታሰቢያቸውን ሁሉ እንዲጠፋ አድርገሃል።
15እግዚአብሔር ሆይ፣ ሕዝብን አበዛህ፣ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፣ የአገሪቱን ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ።
16እግዚአብሔር ሆይ፣ በመከራ ጊዜ ተመለከቱህ፤ ቅጣትህ በእነርሱ ላይ በሆነ ጊዜ ድግምታቸውን ሳይቀር በክፉው ላይ ተናገሩ።
17የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትታመምና በምጥ እንደምትጮኽ፣ አቤቱ፣ እንዲሁ በፊትህ ሆነናል።
18እኛ ፀንሰናል፣ ምጥም ይዞናል፣ ነገር ግን ነፋስን እንደምንወልድ ሆነናል፤ ድነትን ወደምድር አላመጣንም፣ በዓለምም የሚኖሩ አልወደቊም።
19ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፣ ጠልህ የመድሃኒት ጠል ነውና፣ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም።
20ሂድ ሕዝቤ ሆይ፣ ወደ ክፍሎችህ ግባና ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።
21ተመልከት፣ በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቍጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፣ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።