መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 14

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፣ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፣ በገዛ አገራቸውም ያኖራቸዋል። መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፣ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃል።
2አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል። የእስራኤልም ቤት በእግዚአብሔር ምድር እንደ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች አድርገው ይገዙአቸዋል። የማረኩአቸውን ይማርካሉ፣ አስጨናቂዎችንም ይገዛሉ።
3በዚያም ቀን፣ እግዚአብሔር ከኀዘንህና ከመከራህ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል።
4ይህንም ምሳሌ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ፣ "አስጨናቂ እንዴት በፍጻሜው ዐረፈ፣ ኩሩውስ እንዴት ጸጥ አለ!" ይላሉ።
5እግዚአብሔር የአሕዛብ ገዢዎችን በትር በመዓትና በማያቋርጥ መምታት መታ፣
6አሕዛብንም ባልተከለከለ መከራ፣ በቍጣው የገዛውን የኀጥኣንን በትር የአለቆችንም ዘንግ እግዚአብሔር ሰብሮአል።
7ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች፤ በዝማሬ ክብረ-በዓላቸውን ማድረግ ጀምረዋል።
8ጥድና የሊባኖስ ዝግባ፣ 'አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም' ብለው በአንተ ደስ አላቸው።
9ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የሞቱትንም፣ የምድርን ታላላቆች ሁሉ፣ ለአንተ አንቀሳቀሰች፣ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው አስነሣች።
10እነዚህ ሁሉ ተናግረው፣ 'አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃል። እኛን መስለሃል። ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤
11በበታችህም ብል ተነጥፎአል። ትልም ይሸፍንሃል' ብለው ይመልሱልሃል።
12አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፣ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፣ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ!
13አንተ በልብህ፣ 'ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፣ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፣ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤
14ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፣ በልዑልም እመሰላለሁ' አልህ።
15ነገር ግን ወደ ሲኦል፣ ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።
16የሚያዩህ አፍጥጠው ይመለከቱሃልና። በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፣ መንግሥታትንም ያናወጠ፥
17ዓለሙን ሁሉ ባድማ ያደረገ፣ ከተሞችንም ያፈረሰ ምርከኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልሰደደ ሰው ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል።
18የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ፣ በየመቃብራቸው በክብር አንቀላፍተዋል።
19አንተ ግን እንደ ተጠላ ቅርንጫፍ ከመቃብርህ ተጥለሃል፤ በሰይፍም የተወጉት፣ ተገድለውም ወደ ጕድጓዱ ድንጋዮች የወረዱት ከድነውሃል፤ እንደ ተረገጠም ሬሳ ሆነሃል።
20ምድርህን አጥፍተሃልና፣ ሕዝብህንም ገድለሃልና ከእነርሱ ጋር በመቃብር በአንድነት አትሆንም፤ የክፉዎች ዘር ለዘላለም የተጠራ አይሆንም።"
21እንዳይነሡም፣ ምድርንም እንዳይወርሱ፣ የዓለሙንም ፊት በከተሞች እንዳይሞሉ ስለ አባቶቻቸው በደል ለልጆቹ ሞትን አዘጋጁላቸው።
22"በእነርሱ ላይ እነሣለሁ" ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፣ ዘርንና ትውልድንም እቈርጣለሁ ይላል እግዚአብሔር።
23"የጃርት መኖርያ የውኃም መቋሚያ አደርጋታለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ" ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
24የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፣ "እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል።
25አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፣ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ። ከዚያም ቀንበሩ ከእነርሱ ላይ ይነሣል፣ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል።"
26በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት።
27የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው?
28ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት ይህ ዐዋጅ ወጣ።
29ፍልስጥኤም ሆይ፣ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፣ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ።
30የድሆችም የበኵር ልጆች ይሰማራሉ፣ ችግረኞችም ተዘልለው ይተኛሉ፤ ሥርህንም በራብ እገድላለሁ፣ ቅሬታህም ይገደላል።
31አንተ በር ሆይ፣ ወዮ በል አንቺም ከተማ ሆይ፣ ጩኺ፤ ፍልስጥኤም ሆይ፣ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይመጣል ከጭፍራውም ተለይቶ የሚቀር የለም።
32ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መመለስ ይገባል? እግዚአብሔር ጽዮንን እንደ መሠረተ፣ የሕዝቡም ችግረኞች በእርስዋ ውስጥ እንደሚጠጉ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።