1የይሁዳ ነገሥታት በሆኑት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ።
2ስሙ፣ ምድርም አድምጪ፤ "ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፣ እነርሱም አመጹብኝ።" ሲል እግዚአብሔር ተናግሮአልና።
3በሬ የገዢውን፣ አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፥ እስራኤል አልተገነዘበም"
4ወዮላችሁ! ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፣ የክፉ አድራጊዎች ልጆች፣ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ! እግዚአብሔርን ትተዋል፣ የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል።
5አሁን ድረስ ለምን ትቀሰፋላችሁ? አሁንም አሁንም ዓመፃ ለምን ትጨምራላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም፣ ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል።
6ከእግር መርገጫ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ያልታመመ የለውም፤ ቍስልና እበጥ፣ የሚደማ ቊስል ነው፤ አልፈረጠም፣ አልተጠገነም፣ በዘይትም አልለዘበም።
7ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ እንግዶች ይበሉታል፤ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች።
8የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፣ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፣ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች።
9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጥቂት ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፣ እንደ ሰዶም በሆንን፣ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር።
10የሰዶም አለቆች ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፣ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ።
11"የመሥዋዕታችሁ ብዙ ጋጋታ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል?" ይላል እግዚአብሔር። "የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።
12በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ፣ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው?
13ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም - እነዚህን የረከሱ ጉባዔዎች አልታገሥም።
14መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።
15ስለዚህም እጃችሁን በጸሎት ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፣ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።
16ታጠቡ፣ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ መሆንን ተዉ፤
17መልካም ማድረግን ተማሩ፣ ፍርድን ፈልጉ፣ የተጨቆነውን እርዱ፣ አባት ለሌለው ፍረዱለት፣ ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።"
18"አሁን ኑና በአንድ ላይ እንዋቀስ" ይላል እግዚአብሔር፤ "ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን፣ እንደ በረዶ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ፣ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።
19እሺ ብትሉ ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ።
20ነገር ግን እምቢ ብትሉ፣ ብታምፁም፣ ሰይፍ ይበላችኋል፣" የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
21ፍርድ ሞልቶባት የነበረችው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ ሞልቶባት ነበር፣ አሁን ግን ገዳዮች ሞልተውባታል።
22ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፣ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ።
23አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፣ ዋጋም ለማግኘትም ይሮጣሉ። ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፣ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም።
24ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ወዮላቸው! የሚቋቋሙኝ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፣ በጠላቶቼ ላይ እበቀላለሁ።
25እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፣ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፣ አለመንጻትሽንም ሁሉ አወጣለሁ፤
26ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ፣ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ፣ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።"
27ጽዮን በፍርድ፣ ከእርሷም በንስሃ የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ።
28በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፣ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ።
29"በተመኛችኋት የተቀደሰች የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁና፣ በመረጣችኋትም አትክልት ስፍራ ላይ እፍረት ይይዛችኋልና፤
30ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፣ ውሃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና።
31ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፣ ሥራውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ አብረውም ይቃጠላሉ፣ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።"