1በይሁዳ ነገሥታት በዖዚያን፥ በኢዮአታም፥ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን፤በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብዔር ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2እግዚአብሔር በሆሴዕ አማካይነት መናገር በጀመረ ጊዜ እንዲህ አለው፦«ምድሪቱ እኔን በመተው ታላቅ ምንዝርናን እያደረገች ነውና፥ሂድ፥የምንዝርናዋ ፍሬዎች የሆኑ ልጆች ያሏትን ሴተኛ አዳሪዋን ሚስትህ አድርገህ ውሰድ።»
3ስለዚህም ሆሴዕ ሄዶ የዴቤላይምን ሴት ልጅ ጎሜርን አገባ፤እርስዋም ጸነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደችለት።
4እግዚአብሔርም አለው፦ «ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢይዝራኤል ስለነበረው ደም ማፍሰስ የኢዩን ቤት እቀጣለሁና፥ የቤተ እስራኤልንም መንግሥት እንዲያከትም አደርጋለ ሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው።
5ይህም በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት በምሰብርበት ቀን ይፈጸማል።»
6ጎሜር እንደገና ጸነሰች፥ ሴት ልጅም ወለደች። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ «ቅንጣት ታህል ይቅር እላቸው ዘንድ ከእንግዲህ ወዲያ የእስራኤልን ቤት አልምርምና ስሟን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት።
7ነገር ግን የይሁዳን ቤት እምራለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር አምላካችው በራሴ አድናቸዋለሁ እንጂ በቀስት፥ በሰይፍ፥ በጦርነት፥ በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች አላድናቸውም።»
8ጎሜር፥ ሎሩሃማን ጡት ካስጣለቻት በኋላ ጸነሰች፥ሌላ ወንድ ልጅም ወለደች።
9በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፦«ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላካችሁ አይደለሁምና ስሙን ሎዓሚ ብለህ ጥራው ።»
10ነገር ግን የእስራኤል ቤት ቁጥር ሊለካ ወይም ሊቆጠር እንደማይችል የባሕር አሸዋ ይሆናል። «ሕዝቤ አይደላችሁም» በተባሉበት ቦታ፥«የሕያው አምላክ ሕዝብ ናችሁ» ይባላሉ።
11የይሁዳ ሕዝብና የእስራኤል ሕዝብ በአንድነት ይሰበሰባሉ። የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና፥ ለራሳቸው አንድ መሪ ይሾማሉ፥ ከምድሪቱም ይውጣሉ።