1በሰባተኛው ወር፣ ከወሩም በሃያ አንደኛው ቀን የያህዌ ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል መጣ እንዲህም አለ፤
2“ለይሁዳ ገዢ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤልና ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለካህኑ ኢያሱ፣ እንዲሁም ከምርኮ ለተረፉት ሰዎች ተናገሩ እንዲህም በሏቸው
3የዚህን ቤት የቀድሞ ክብር ያየ በመካከላችሁ ማን አለ? አሁንስ እንዴት ሆኖ ይታያችኋል? በዓይኖቻችሁ ፊት እንደ ተራ ነገር ቀልሎ የለምን?
4አሁንም ዘሩባቤል ሆይ፣ በርታ! ይህ የያህዌ ዐዋጅ ነው አንተም የኢዮሴዴቅ ልጅ ሊቀ ካህኑ ኢያሱ በርታ፤ በምድሪቱ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ በርቱ! - ይህ የያህዌ ዐዋጅ ነው፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ተነሡ ሥሩ! ይህ የሠራዊት ጌታ የያህዌ ዐዋጅ ነው
5ከግብፅ በወጠችሁ ጊዜ በገባሁላችሁ ኪዳን፣ በመካከላችሁም ባለው መንፈሴ አትፍሩ!
6የሠራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፤ በቅርብ ጊዜ ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕርንና ደረቁን ምድር አናውጣለሁ!
7ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ ሕዝቦች የከበሩ ነገሮቻቸውን ወደ እኔ ያመጣሉ፤ ይህንንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ! ይላል የሠራዊት ጌታ ያህዌ።
8ብርና ወርቁ የእኔ ነው! ይህ የሠራዊት ጌታ የያህዌ ዐዋጅ ነው።
9የወደፊቱ የዚህ ቤት ክብር ከመጀመሪያው ይበልጣል ይላል የሠራዊት ጌታ ያህዌ፤ በዚህ ቦታ ሰላም እሰጣለሁ - ይህ የሠራዊት ጌታ የያህዌ ዐዋጅ ነው።”
10ዳርዮስ በነገሠ ሁለተኛው ዓመት፣ በዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን የያህዌ ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል መጣ፤ እንዲህም አለ፣
11“የሠራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፤ ሕጉ ምን እንደሚል ካህናቱን ጠይቁ፤
12አንድ ሰው ለያህዌ የተቀደሰውን ሥጋ በልብሱ እጥፋት ቢይዝ፣ በልብሱ እጥፋት እንጀራ ወይም ወጥ፣ የወይን ጠጅ ወይም ዘይት ወይ ሌላ ምግብ ቢነካ፣ ያ ምግብ ይቀደሳልን?” ካህናቱም፣ “የለም፣ አይቀደስም” በማለት መለሱ።
13ሐጌም፣ “ሬሳ በመንካቱ የረከሰ ሰው ከእነዚህ አንዱን ቢነካ ይረክሳሉን?” አለ። ካህናቱም፣ “አዎን፣ ይረክሳሉ” በማለት መለሱ።
14ስለዚህ ሐጌ መልሶ፣ “ ይህም ሕዝብ በፊቴ እንዲሁ ነው! - ይህ የያህዌ ዐዋጅ ነው፤ የእጃቸው ሥራና ለእኔ የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው።
15እንግዲህ ከዘሬ ጀምራችሁ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ ልብ በሉ፤
16ለምሆኑ ያኔ እንዴት ነበር? አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ እህል ጠብቆ ወደ ክምሩ ሲሄድ አሥር ብቻ አገኘ። አምሳ ማድጋ ወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው ሲሄድ ሃያ ብቻ አገኘ።
17እናንተንና የእጆቻችሁን ሥራ ሁሉ በዋግና በአረማሞ መታሁ፤ ያም ሆኖ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም - ይህ የያህዌ ዐዋጅ ነው።
18ከዚህ ቀን ጀምሮ ማለትም የያህዌ ቤተመቅደስ መሠረት ከተጣለበት ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛው ቀን ጀምሮ ወደፊት ቁጠሩ፤ ልብ አድርጋችሁ አስቡት!
19በጎተራው የቀረ ዘር ይኖራልን? የወይኑና የበለሱ፣ የሮማኑና የወይራው ዛፍ ፍሬ አላፈሩም! ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ!”
20በዘጠነኛው ወር በወሩም ሃያ አራተኛ ቀን የያህዌ ቃል በድጋሚ ወደ ሐጌ መጣ፤ እንዲህም አለ፣
21“ለይሁዳ ገዥ ለዘሩባቤል እንዲህ በለው፤ “ሰማያትንና ምድርን አናውጣለሁ።
22የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የሕዝቦችን መንግሥት ብርታት አጠፋለሁ! ሰረገሎችንና በላያቸው ያሉትን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ጋላቢዎቻቸውን በገዛ ወንድሞቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።
23በዚያ ቀን - የሠራዊት ጌታ የያህዌ ዐዋጅ እንዲህ የሚል ይሆናል- የሰላትያል ልጅ ባርያዬ ዘሩባቤል ሆይ፣ እኔ እወስድሃለሁ፤ ይህ የያህዌ ዐዋጅ ነው። እኔ መርጬሃለሁና ቀለበቴ ላይ እንደ ማህተም አደርግሃለሁ፤ ይህ የሠራዊት ጌታ የያህዌ ዐዋጅ ነው።