1ይስሐቅ አርጅቶ ዐይኖቹም ታውረው ነበር፤ ታላቁ ልጁን ዔሳውን፤ "ልጄ ሆይ!" ብሎ ጠራው፤ ልጁም "እነሆ አለሁ" አለ።
2ይስሐቅም እንዲህ አለው፣ "እንደምታየኝ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም፤
3ስለዚህ የምታድንበትን ቀስትና ፍላጻ ያዝ፤ ወደ ዱር ሂድና አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤
4ልክ እንደምወደው አድርገህ ምግብ ሥራልኝ ከበላሁም በኋላ ከመሞቴ በፊት የመጨረሻ ምርቃቴን እሰጥሃለሁ።"
5ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ወደ አደን ከሄደ በኋላ፣
6ርብቃ ልጅዋን ያዕቆብን "አባትህ ዔሳውን እንዲህ ሲለው ሰማሁ፣
7አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤ ልክ እንደምወደው አድርገህ የጣፈጠ ምግብ ሥራልኝ፤ ሳልሞትም በእግዚአብሔር ፊት እነርቅሃለሁ፤
8አሁንም ልጄ ሆይ! የምነግርህን አድምጥ፤ የማዝህንም አድርግ፤
9አባትህ እንደሚወደው አጣፋጩ ጥሩ ምግብ እንድሠራለት፣ ወደ መንጋዎች ሂድና ሁለት የሰቡ የፍየል ጥቦቶች አምጣልኝ፤
10አንተም ያዘጋጀሁትን ምግብ እንዲበላ ለአባትህ ወስደህ ታቀርብለታለህ፤ በዚህ ዐይነት አባትህ ከመሞቱ በፊት ይመርቅሃል።"
11ያዕቆብ ግን እናቱን ርብቃን "የወንድሜ የዔሳው ገላ ጠጉራም ነው፤ የ እኔ ገላ ግን ምንም ጠጉር የሌለው ለስላሳ ነው፤
12ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝና እንዳታለልኩህ ቢያውቅ በምርቃት ፈንታ እርግማን እንደማተርፍ ታውቂ የለምን?" አላት።
13እናቱም "ልጄ ሆይ! የአንተ እርግማን በእኔ ላይ ይሁን፤ አሁንም እንደነገርሁህ አድርግ፤ ሄድህ ጥቦቶቹን አምጣልኝ" አለችው።
14ስለዚህ ሄዶ ጥቦቶቹን አመጣለት እርስዋም ልክ አባቱ እንደሚወደው እድርጋ ጥሩ ወጥ ሠራች፤
15የታላቁ ልጅዋን የዔሳውን የክት ልብስ ከተቀመጠበት ቦታ አውጥታ ለያዕቆብ አለበሰችው።
16የፍየሎቹንም ቆዳ በክንዶቹ ላይና ጠጉር በሌለበት በአንገቱ ላይ አለበሰችው።
17ያዘጋጀውንም ጥሩ ወጥ ከጋገረችው እንጀራ ጋር ልልጅዋ ለያዕቆብ ሰጠችው።
18ያዕቆብ ወደ አባቱ ሄደና "አባባ!" አለው፤ እርሱም "እነሆ አለሁ! ለመሆኑ አንተ የትኛው ልጄ ነህ!" አለ።
19ያዕቆብም "የበኩር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ እነሆ እንዳዘዝከኝ አድርጌአለሁ፤ እንድትመርቀኝ እስቲ ቀና በልና ያመጣሁልህን የአደን ሥጋ ተመገብ" አለው።
20ይስሐቅም "ልጄ ሆይ! እንዴት ቶሎ ልታገኝ ቻልህ?" አለው። ያዕቆብም "አምላክህ እግዚአብሔር ስለረዳኝ በቶሎ ለማግኘት ቻልሁ" አለው።
21ይስሕቅም "እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በልና ልዳብስህ፤ በእርግጥ አንተ ዔሳው ነህን?" አለው።
22ያዕቆብም ወደ አባቱ ተጠጋ፤ አባቱም ዳሰሰውና "ድምፅህ የያዕቆብ ድምፅ ይመስላል፤ ክንድህ ግን የዔሳውን ክንድ ይመስላል" አለው።
23ክንዶቹ እንደ ዔሳው ክንዶች ጠጉራም ስለ ነበሩ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማውቅ አልቻለም፤ ሊመርቀው ከዝዘጋጀ በኋላ፣
24"እርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?" ሲል እንደገና ጠየቀው፤ እርሱም "አዎ ነን" አለ።
25ይስሐቅም "ልጄ! በል ከአደንከው ሥጋ አቅርብልኝ፤ ከበላሁም በኋላ እመርቅህለሁ" አለው። ያዕቆብም ምግቡን አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም እንዲጠጣ አመጣለት።
26ከዚህ በኋላ አባቱ ይስሐቅ "ልጄ ሆይ! ቀረብ በልና ሳመኝ" አለው፤
27ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው። ይስሐቅ የያዕቆብ ልብስ ባሸተተ ጊዜ እንዲህ ሲል መረቀው፣ "እነሆ የልጄ መልካም ሽታ እግዚአብሔር እንደባረከው የእርሻ ሽታ ነው፤
28እግዚአብሔር ከሰማይ የሚያረሰርሰው ተል ይስጥህ፤ ምድርህን ያለምልምልህ፤ እህልንና የወይን ጠጅህን ያብዛልህ፤
29መንግሥታት ይገዙልህ፤ ሕዝቦችህም ያገልግሉህ፤ በወንድሞችህ ሁሉ ላይ አለቃ ሁን፤ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤ የሚመርቁህ የተመረቁ ይሁኑ።"
30ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃና ያዕቆብም አባቱን ፊት እንደወጣ ወዲያውኑ ዔሳው ከአደን ተመልሶ መጣ።
31እርሱም በበኩሉ የጣፈጠ ወጥ ሠርቶ ለአባቱ አቀረበለትና "አባቴ ሆይ እንድትመርቀኝ፣ እስቲ ቀና ብለህ ካመጣሁልህ የአደን ሥጋ ብላ" አለው።
32ይስሐቅም 'አንተ ማን ነህ?" አለው፤ እርሱም "እኔ የበኩር ልጅ ዔሳው ነኝ" አለ።
33ይስሐቅም እጅግ ደንግጦ እየተነቀጠቀጠ "ታዲያ አውሬ አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበረ? ልክ አንተ ከመምጣትህ በፊት ተመገብሁ የመጨረሻ ምርቃቴንም ሰጠሁት፤ ምርቃቱም ተእርሱ ሆኖ ይኖራል"አለው።
34ዔሳው ይህን በሰማ ጊዜ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ እያለቀሰ "አባቴ ሆይ! እኔንም መርቀኝ!" አለ።
35ይስሐቅም "ወንድምህ መጥቶ እኔን በማታለል የአንተን ምርቃት ወስዶብሃል"አለው።
36ዔሳውም "እርሱ እኔን ሲያሰናክለኝ ይህ ሁለተኛው ነው፤ ያዕቆብ መባሉ ተገቢ ነው፤ ከዚህ በፊት ብኩርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ፤ ታዲያ ለእኔ ያስቀረከው ምንም ምርቃት የለምን? አለው።
37ይስሐቅም "ቀድሞ ብዬ እርሱን የአንተ ጌታ አድርጌዋለሁ፤ ወንድሞቹ ሁሉ የእርሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጌአለሁ፤ እህልና የወይን ጠጅ እንዲበዛለት አድርጌአለሁ፤ ልጄ ሆይ! እንግዲህ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?" አለው።
38ዔሳውም "አባቴ ሆይ! ምርቃትህ እንዲት ብቻ ናትን? እባክህ እኔንም መርቀኝ" እያለ ለማልቀስ አባቱን ነዘነዘው።
39ይስሐቅም አንዲህ አለው። "በረከት ከሞላበት ለምለም ምድር ርቀህ ትኖራለህ፤ የሰማይ ጠልም አታገኝም፤
40በሰይፍም ኅይል ትኖራለህ፤ የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ፤ በተቃወምከውም ጊዜ ግን ከእርሱ ጭቁና ትላቀቃለህ።"
41አባቱ ስለመረቀው ዔሳው ያዕቆብን አጥብቆ ጠላው፤ በልቡም "አባቴ በቅርብ ቀን ይሞታል፤ ከዚህ በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ"ብሎ አሰበ።
42ነገር ግን ርብቃ የዔሳውን ዕቅድ ስለ ሰማች፣ ያዕቆብን ጠርታ እንዲህ አለችው፣ "አድምጠኝ፤ ወንድምህ ዔሳው አንተን በመግደል ሊበቀልህ አስቦአል፤
43አሁንም ልጄ ሆይ! የምልህን አድርግ፤ ተነሥተህ በካራን ወደሚገኘው ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሽሽ፤
44የወንድምህ ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እዚያው ቆይ፤
45ቁጣውም ሲበርድ ያደረግህበትን ነገር ይረሳል፤ ከዚያ በኋላ ሰው ልኬ አስመጣሃለሁ፤ ሁለታችሁም በአንድ ቀን ማጣት አልፈልግም።
46ርብቃ ይስሐቅን "ዔሳው ባገባቸው በእነዚህ በሖታውያን ሴቶች ምክንያት መኖሬን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ደግሞ ከነዚህ ከሒታውያን ሴቶች አንዲቱ ከገባ ለመኖር ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ"አለችው።