1ወንድሞች ሆይ አንድ ሰው ስቶ ቢገኝ መንፈሳዊያን የሆናችሁ እናንት በጨዋነት መንፈስ ልታቀኑት ይገባል።ወደ ፈተና እንዳትገቡ ለራሳችሁም ተጠንቀቁ።
2የእርስ በእርሳችሁን ሸክም በመሸካከም የክርስቶስን ህግ ፈጽሙ።
3ምክንያቱም ማንም ምንም ሳይሆን ምንም እንደሆነ ቢያስብ ራሱን ያታልላል።
4እያንዳንዱ ከሌላው ጋር ሳያነጻጽር የራሱን ሥራ ሊመዝን ይገባል፥ያን ጊዜ የሚመካበት ሊያገኝ ይችላል።
5እያንዳንዱ የየራሱን ሸክም ይሸከማልና።
6ቃሉን የሚማር ከመምህሩ ጋር ሁሉን ነገር ይካፈል ዘንድ ይገባዋል።
7አትታለሉ እግዚአብሔር አይቀለድበትም።ሰው ምንም ነገር ቢዘራ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል።
8በሥጋው የሚዘራ ከሥጋው ውድቀትን ያጭዳል፤በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ህይወት ያጭዳል።
9በተገቢው ጊዜ ፍሬውን እናጭዳለንና መልካምን ከመስራት አንቦዝን።
10ስለዚህም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለሰው ሁሉ በተለይም ለእምነት ቤተሰቦች መልካምን እናድርግ።
11በገዛ እጅ ጽህፈቴ ምን ዓይነት ትልልቅ ቃላት እንደጻፍኩላችሁ ተመልከቱ።
12እነዚያ በሥጋ መልካም መስለው የሚታዩ ስለክርስቶስ መስቀል መከራ ላለመቀበል ብለው እንድትገረዙ ያስገድዱዋችኋል።የተገረዙት እራሳቸው ህጉን አይጠብቁ፣
13ነገር ግን እናንተን እንድትገረዙ በማድረጋቸው ጉራ ለመንዛት እንድትገረዙ ይፈልጋሉ።
14ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት እኔም ለዓለም ከተሰቀልኩበት ከክርስቶስ መስቀል በስተቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።
15አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም።
16በዚህ ሥርዓት ለሚሄዱ ሁሉ እንዲሁም የእግዚአብሔር ለሆነችው ለእስራኤል ሠላምና ምህረት ይሁን።
17የክርስቶስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ማንም አይረብሸኝ።
18ወንድሞች ሆይ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁጋር ይሁን። አሜን!