1የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በነገሠበት የመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር በኤርምያስ አፍ የተነገረውን ቃሉን ፈጸመና የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ። የቂሮስ ድምጽ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ተሰማ። የተነገረውና የተጻፈው እንዲህ የሚል ነው፤
2"የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድር መንግሥታትን ሁሉ ሰጥቶኛል፥ በይሁዳ ባለች በኢየሩሳሌም ቤት እንድሠራለት አዞኛል።
3ማንም ከሕዝቡ ጋር የሚመጣ ቢኖር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና የኢየሩሳሌም አምላክ ለሆነው ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ።
4የሚቀሩት በሚኖሩባቸው በመንግሥቱ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ብርና ወርቅ፥ ንብረትና እንስሳ በተጨማሪም በኢየሩሳሌም ላለው የእግዚአብሔር ቤት የበጎ ፈቃድ ቁርባን ይስጡ"።
5ከዚያም የይሁዳና የብንያም ነገድ የቤተሰብ አለቆች፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑና እንዲሄዱና ቤቱን እንዲሠሩለት እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣ ሁሉ ተነሡ።
6በዙሪያቸው ያሉትም ሥራቸውን በብርና ወርቅ ዕቃ፥ በቁሳቁስ፥ በእንስሳ፥ በጠቃሚ ዕቃዎችና በበጎ ፈቃዳቸው በሰጡት መባ አገዟቸው።
7ደግሞም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም አምጥቶ በአማልክቶቹ ቤቶች ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ንጉሡ ቂሮስ አወጣቸው።
8ቂሮስ በግምጃ ቤቱ ኃላፊ በሚትሪዳጡ እጅ ሰጠ፥ እርሱም ለይሁዳው አለቃ ለሰሳብሳር ቆጥሮ አስረከበው።
9ብዛታቸው እንደሚከተለው ነበር፤ ሠላሳ የወርቅ ሳሕን፥ አንድ ሺህ የብር ሳሕን፥ ሃያ ዘጠኝ ሌሎች ሳሕኖች።
10ሠላሳ ጎድጓዳ የወርቅ ሳሕን፥ 410 ትናንሽ ጎድጓዳ የብር ሳሕኖችና ሌሎች አንድ ሺህ ዕቃዎች ነበርሩ። በአጠቃላይ 5400 የብርና የወርቅ ዕቃዎች ነበሩ።
11ምርኮኞቹ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በሄዱ ጊዜ እነዚህን ሁሉ ሰሳብሳር አመጣቸው።