መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሕዝቅኤል 47

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና ውኃውም ከመስዊውው በስተቀኝ በኩል ወደ ቤተመቅደሱ ደቡብ አቅጣጫ ይወርድ ነበር።
2በሰሜኑም በር በኩል አወጣኝ በስተ ውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በስተ ውጭ ወዳለው በር መራኝ እነሆም፥ ውኃው ከበሩ ምዕራብ ወገን ይፈስስ ነበር።
3ሰውዬውም ገመዱን በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ አንድ ሺህም ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃም እስከ ቍርጭምጭሚት ደረሰ።
4ደግሞ አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ጕልበት ደረሰ። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ደረሰ።
5ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ።
6ሰውዬውም፥ "የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን?" አለኝ። አመጣኝም፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ።
7በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ።
8እርሱም እንዲህ አለኝ፥ "ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ጨው ባሕሩም ወደ መልካም ውሃነቱ ይመልሰዋል።
9ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ወንዙ በመጣበት ስፍራ ሁሉ በሕይወት ይኖራል ይህም ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ። ጨዋማ ባህርን መልካም ያደርጋል። ወንዙም በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል።
10የዓይንጋዲ አጥማጆችም በወንዙ ዳር ይቆማሉ በዓይንጋዲ መረብ መዘርጊያ ቦታ ይገኛል። በጨው ባህርም ዓሣዎች እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣዎች በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ።
11ነገር ግን የጨው ባህር እረግረጉና እቋሪው ሥፍራ ጨው ለመስጠት ጨዋማ እንደ ሆነ ይኖራል እንጂ አይቀየርም።
12በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል። ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይቋረጥም። ውኃውም ከመቅደስ የሚመጣ በመሆኑ ዛፎቹ በየወሩ ፍሬ ያፈራሉ። ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል።
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ርስት አድርጋችሁ ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት እንደዚህ ነው፡ ለዮሴፍ ሁለት እድል ፈንታ ይሰጠዋል።
14ለአባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ ምዬ ነበርና እናንተ እያንዳንዳችሁ እኩል አድርጋችሁ ትካፈላላችሁ። በዚህም መንገድ ይህች ምድር ርስት ትሆናችኋለች።
15የምድሪቱም ድንበር ይህ ነው። በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጽዳድ መግቢያ
16ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን።
17ስለዚህም ድንበሩ ከባሕሩ በደማስቆ ድንበር ላይ ያለው ሐጸርዔናን ሐማት ድንበር ይሆናል። ይህ የሰሜኑ ድንበር ነው።
18የምሥራቁም ድንበር በሐውራን በደማስቆና በገለዓድ በእስራኤልም ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል። ይህም ድንበር እስከ ታማር ድረስ ይሄዳል።
19የደቡቡም ድንበር ከደቡብ ታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። የደቡቡ ድንበር ይህ ነው።
20የምዕራቡም ድንበር ከታላቁ ባሕር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ይሆናል። የምዕራቡ ድንበር ይህ ነው።
21እንዲሁ ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገድነታችሁ ለእናንተ ትካፈላላችሁ።
22ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ እንደአገር ልጆች ላሉ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ ። በእስራኤልም ነገዶች መካከል ለርስት ክፍፍል ዕጣ ትጣላላችሁ።
23መጻተኛውም በማናቸውም ነገድ መካከል ቢቀመጥ በዚያ ርስቱን ትሰጡታላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።