መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሕዝቅኤል 45

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ርስትም አድርጋችሁ ምድሪቱን በዕጣ በምታካፍሉበት ጊዜ ለእግዚአብሔር መባ ታቀርባላችሁ። ይህም መባ የምድሪቱ የተቀደሰ ሥፍራ ሲሆን ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል በዳርቻው ሁሉ ዙሪያውን የተቀደሰ ይሆናል።
2ከእርሱም ርዝመቱ አምስት መቶ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ አራት ማዕዘን የሆነ ቦታ ለመቅደሱ ይሆናል በዙሪያውም ባዶ ስፍራ የሚሆን አምሳ ክንድ ይሆናል።
3ከዚያ ቦታ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም አሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ትለካለህ፤ እርሱም ቅዱስ ስፍራና ቅድስተ ቅዱሳን ይሆንልሀል።
4ከምድሪቱም እግዚአብሔርን ለሚያገለግሉና ሊያገለግሉትም ወደ እግዚአብሔር ለሚቀርቡት ለካህናት የተለየ ክፍል ይሆናል። ለቤቶቻቸውም የሚሆን ስፍራ ለመቅደስም የሚሆን የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል።
5ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ስፍራ ለቤቱ አገልጋዮች ለሌዋውያን ይሆናል፥ ለሚቀመጡባቸውም ከተሞች ለራሳቸውም የርስት ይዞታ ይሆናል።
6ለከተማ የሚሆን ሥፍራም ከተቀደሰው የዕጣ ክፍል አጠገብ ወርዱ አምስት ሺህ ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ የሆነውን ስፍራ ትለያላችሁ። ይህም ከተማ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይሆናል።
7ለአለቃ ይዞታ የሆነው የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል። በምዕራብና በምሥራቅ ይሆናል። ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል።
8ይህም ለእስራኤል አለቃ ይዞታ ይሆንለታል። አለቆቼም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም።
9ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል አለቆች ሆይ፥ ይብቃችሁ ግፍንና ብዝበዛን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ! ሕዝቤን መቀማት አቁሙ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር!
10እውነተኛ ሚዛን እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ እውነተኛውም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ።
11የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ መጠናቸው እኩል ሆኖ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አንድ አሥረኛ ይሆናል ፥ መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን።
12ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ይሁን ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል፥ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ።
13የምታቀርቡት መባ ይህ ነው ከአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ የኢፍ መስፈሪያ አንድ ስድስተኛ፥ ከአንድም ቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የኢፍ መስፈሪያ አንድ ስድስተኛ ትሰጣላችሁ።
14የዘይቱም ደንብ፥ ከእያንዳንዱ የቆሮስ መስፈሪያ የባዶስን አንድ አሥረኛ ወይም ለእያንዳንዱ ቆሮስ ምክንያቱም አሥር የባዶስ መስፈሪያ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ነው።
15ውኃም ካለበት ከእስራኤል አውራጃ ከመንጋው ከሁለቱ መቶ አንዱን የበግ ጠቦት ትሰጣላችሁ ይህ ያስተሰርይላችሁ ዘንድ ለእህል ቍርባንና ለሚቃጠል መሥዋዕት ለደኅንነትም መሥዋዕት ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
16የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይህን መባ ለእስራኤል አለቃ ይሰጣሉ።
17በየበዓላቱም በየመባቻውም በየሰንበታቱም በእስራኤልም ቤት ዓመት በዓል ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የመጠጡንም ቍርባን በየመደቡ ማዘጋጀት የአለቃው ይሆናል። እርሱ የእስራኤል ቤት ወክሎ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርባል።
18ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ ስለ መቅደሱም የኃጢአት መስዋዕት ታቀርባላችሁ።
19ካህኑም ከኃጢአቱ መሥዋዕት ደም ወስዶ በመቅደሱ መቃኖችና በመሠዊያው እርከን በአራቱ ማዕዘን በውስጠኛውም አደባባይ በበሩ መቃኖች ላይ ይርጨው.
20ይህንንም ከወሩ በሰባተኛው ቀን ስለ ሳተውና ስላላወቀው ታደርጋለህ። በዚህ መንገድ ለቤተ መቅድሱ ታስተስርያላችሁ።
21በመጀመሪያ ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታደርጋላችሁ። የሰባት ቀንም በዓል ይሆናል። የቂጣ እንጀራም ትበላላችሁ።
22በዚያም ቀን አለቃው ለራሱና ለአገሩ ሕዝብ ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ያቀርባል።
23በበዓሉም በሰባቱ ቀኖች የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፡ ሰባቱንም ቀኖች በየዕለቱ ነውር የሌለባቸውን ሰባት ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ያቅርብ ለኃጢአትም መሥዋዕት በየዕለቱ አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ።
24ለአንድም ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህል ቍርባን ያቅርብ።
25አለቃው በሰባተኛውም ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በበዓሉ ሰባት ቀኖች፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የእህሉንም ቍርባን ከዘይቱ ጋር እንዲሁ ያቅርብ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።