መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዘጸአት 40

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
2“በዐዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር የመጀመሪያ ቀን ማደረያውን፣ የመገናኛውን ድንኳን ትከለው።
3ታቦት በውስጡ አስቀምጠው፤ ታቦቱንም በመጋረጃ ከልለው።
4ጠረጴዛውንም ወደ ውስጥ አምጣና በላዩ የሚቀመጡትን ዕቃዎች በሥርዐት አስቀምጥ። ከዚያም መቅረዙን አስገብተህ መብራቶቹን አስተካክል።
5የወርቅ የዕጣን መሠዊያውን በምስክሩ ታቦት ፊት አስቀምጥ፤ የመገናኛውን ድንኳን መግቢያ መጋረጃም አድርግ።
6የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን መሠዊያ በማደሪያው፣ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት አስቀምጥ።
7ትልቁን የመታጠቢያ ሳሕን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠው፤ ውሀም አድርግበት።
8በዙሪያውም አደባባይ ሥራለትን በአደባባዩ መግቢያ ላይ መጋረጃውን ስቀል።
9መቅቢያ ዘይቱን ውሰድና መገናኛውን ድንኳንና አውስጡ ያለውን ዕቃ ሁሉ ቅባ። እርሱንና በውስጡ ያለውን ዕቃ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከዚያም የተቀደሰ ይሆናል።
10የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን መሠዊያና የመሠዊያውን ዕቃዎች ሁሉ ቅባቸው።
11መሠዊያውን ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከዚያም ለእኔ እጅግ የተቀደሰ ይሆንልኛል።
12ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ አምጣና በውሀ እጠባቸው።
13ለእኔ የተቀደሱ ልብሶችን ለአሮን አልብሰው፤ ካህኔ ሆኖ እንዲያገለግልም ቅባው፤ ቀድሰውም።
14ልጆቹንም አምጣና ሸሚዞችን አልብሳቸው።
15ካህናቴ ሆነው እንዲያገለግሉኝ፣ አባታቸውን እንደ ቀባኸው እነርሱንም ቅጣቸው። የእነርሱ መቀባት በትውልዶች ሁሉ የዘለቄታ ካህንነትን ለእነርሱ ያስገኛል።”
16ሙሴ ያደረገው ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ተከተለ። እነዚህንም ሁሉ አደረገ።
17በሁለተኛው ዓመት የመጀመሪያ ወር አንደኛ ቀን ላይ የመገናኛው ድንኳን ተተከለ።
18ሙሴ መገናኛውን ድንኳን ተከለ፤ መቆሚያዎቹንም በስፍራቸው አስቀመጠ፤ ወጋግራዎቹን አቁሞ አግዳሚዎቹን አያያዘ፤ ምሰሶዎቹንም አቆመ።
19በማደሪያው ላይ መሸፈኛውን ዘረጋ፤ ድንኳኑንም እግዚአብሔር አዝዞት እንደ ነበረው ከበላዩ አስቀመጠው።
20ምስክሩን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አስቀመጠው።
21ወደ መገናኛው ድንኳን አመጣው። እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት እንደ ነበረው፣ የምስክሩን ታቦት ለመከለል መጋረጃውን አደረገ።
22ሰሜን ጎን ከመጋረጃው ውጭ ጠረጴዛውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ።
23እግዚአብሔር አዝዞት እንደ ነበረው፣ ኅብስቱን በጠረጴዛው ላይ በሥርዐት በእግዚአብሔር ፊት አስቀመጠው።
24መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ደቡብ ጎን ከጠረጴዛው ትይዩ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ አስቀመጠው።
25መብራቶቹን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በእግዚአብሔር ፊት አበራቸው።
26የተሠራውን የዕጣን መሠዊያም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው ፊት ለፊት አደረገው።
27ላይም እግዚአብሔር አዝዞት እንደ ነበረው ጣፋጭ መዐዛ ያለውን ዕጣን አቀጣጠለ።
28መጋረጃውን በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ሰቀለ።
29የሚቃጠለውን መሥዋዕት መሠዊያም በማደሪያው፣ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ አስቀመጠ። በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አቀረበ።
30የመታጠቢያ ሳሕኑን በመገናኛው ድንኳንና በመሠውያው መካከል አኖረው፤ የመታጠቢያ ውሀም በውስጡ አደረገ።
31ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በመታጠቢያው ውሀ ይታጠቡ ነበር፤
32መገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚገቡትና መሠዊያው ወዳለበት ወደ ላይ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ታጥበውታል።
33ሙሴ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው ዙሪያ አደባባዩን አቆመ። መጋረጃውንም በአደባባዩ መግቢያ ዘረጋ። ሙሴ በዚህ መንገድ ሥራውን ፈጸመ።
34ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፤ የእግዚአብሔር ክብርም ማደሪያውን ሞላው።
35ደመናው በላዩ ስላረፈና የእግዚአብሔር ክብርም ማደሪያውን ስለ ሞላው፣ ሙሴ መገናኛው ድንኳን ውስጥ መግባት አልቻለም ነበር።
36ከማደሪያው ድንኳን በተነሣ ጊዜ ሁሉ፣ የእስራኤል ሰዎች ይጓዛሉ።
37ግን ደመናው ከማደሪያው ላይ ካልተነሣ፣ ሕዝቡ አይጓዙም። ደመናው እስከሚነሣበት ቀን ድረስ ይቆያሉ።
38በሁሉም የእስራኤል ሕዝብ ፊት በጕዟቸው ሁሉ ቀን የእግዚአብሔር ደመና፣ ማታ ደግሞ እሳቱ በማደሪያው ላይ ነበረ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።