መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መክብብ 12

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አስቸጋሪዎቹ ቀናት ሳይመጡ፥ "ደስ አያሰኙኝም" የምትላቸው ዓመታትም ሳይደርሱ፥
2የፀሐይ፥ የጨረቃና የከዋክብት ብርሃን ሳይጨልም፥ የጠቆረው ደመና ከዝናብ ኋላ ሳይመለስ፥ በወጣትነት ዘመንህ ፈጣሪህን አስብ።
3ያ ጊዜ የቤተ መንግሥት ጠባቂዎች የሚርበደበዱበት፥ ብርቱዎች የሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች በመሆናቸው የሚፈጩት ሥራቸውን የሚያቆሙበት፥ በመስኮት ወደ ውጪ የሚመለከቱ አጥርተው የማያዩበት፥ ይሆናል።
4ያ ጊዜ በጎዳናው ላይ በሮች የሚዘጉበትና የወፍጮ ድምጽ የሚቆምበት፥ ከወፍ ድምጽ የተነሣ ሰዎች የሚደነግጡበትና የሚዘምሩ ልጃገረዶች ድምጻቸው ዝግ የሚልበት ይሆናል።
5ያ ጊዜ ሰዎች ከፍታዎችንና በመንገድ ላይ የሚገጥማቸውን አደጋ በማሰብ የሚፈሩበት፥ የለውዝ ዛፍ ሲያብብ፥ አንበጣዎች ተከታትለው ሲሳቡ፥ ተፈጥሯዊ ፍላጎት የሚጠፋበት ጊዜ ነው። ሰው ወደ ዘላለም ቤቱ ይሄዳል፥ አልቃሾችም በጎዳናዎቹ ላይ ይወርዳሉ።
6የብር ሰንሰለት ሳይበጠስ ወይም ጎድጓዳው የወርቅ ሳሕን ሳይሰበር ወይም እንስራው በምንጩ አጠገብ ብትንትኑ ሳይወጣ ወይም የውሃ ማውጫው ጉድጓዱ ውስጥ ሳይበጠስ፥
7አፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስና መንፈስም ወደ ሰጪው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።
8አስተማሪው፥ "የሚተን እንፋሎት፥ ሁሉም ነገር የሚጠፋ እንፋሎት ነው" ይላል።
9አስተማሪው ጠቢብ ነበር፥ ለሕዝቡም እውቀትን አስተማረ። ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና አጠና፥ በስርዓትም አስቀመጣቸው።
10አስተማሪው ግልጽና ቅን የእውነት ቃላትን በመጠቀም ለመጻፍ ፈለገ።
11የጠቢባን ቃል አንደ ከብት መንጃ አርጩሜ ነው። ጠልቀው እንደ ገቡ ሚስማሮች አንድ እረኛ ያስተማራቸውና አስተማሪዎች የሰበሰቧቸው ምሳሌዎችም እንዲሁ ናቸው።
12ልጄ ሆይ፥ በይበልጥ አንድ ነገር ተጠንቀቅ፡ ብዙ መጻሕፍት መጻፍ ማለቂያ የለውም። ብዙ ማጥናትም ሰውነትን ያደክማል።
13ሁሉም ነገር ከተሰማ በኋላ የጉዳዩ መጨረሻ እግዚአብሔርን እንድትፈራውና ትዕዛዙን እንድትጠብቅ ነው፥ ይህ የሰው ሙሉ ተግባሩ ነውና።
14መልካምም ይሁን ክፉ፥ የተደረገውን ሁሉ፥ ከተሰወረው ነገር ሁሉ ጋር፥ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።