1ተመልሰን በባሳን መንገድ ሄድን፥ የባሳን ንጉሥ ዐግና ሕዝቡ ሁሉ በኤድራይ ሊዋጉን መጡ።
2እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአለሁና አትፍራው። በሐሴቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴሶን ላይ እንዳደረግህ በእርሱም ታደርግበታለህ አለኝ።
3እግዚአብሔር አምላካችንም በባሳን ንጉሥ በዐግ ሕዝቡንም ሁሉ በእጃችን ድልን ሰጠን። እኛም አንድ እንዳይቀር እስኪሞቱ ድረስ መታነው።
4በዚያን ጊዜም አንድም ያልወሰድነው ሳይቀር ሁሉንም ስድሳ ከተሞችን፦ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አገር ሁሉ ከተሞችን ወሰድን።
5እነዚህም ከተሞች ሁሉ ዙሪያቸው በረጅም ቅጥር፥ በበሮቻቸውና በመወርወሪያዎች የተመሸጉ ነበር፤ በአጠገባቸውም ብዙ ያልተመሸጉት ከተሞች ነበሩ።
6በሐሴቦንም ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግን ከወንዶችና ሴቶች ከሕፃናትም ጋር ፈጽሞ አጠፋናቸው።
7ነገር ግን ከአጠፋናቸው ከተሞች ሁሉ ከብቶቹን ሁሉ ምርኮም ለራሳችን ወሰድን።
8በዚያም ጊዜ ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ ምድሪቱን ከዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩ ከሁለቱ ከአሞራውያን ነገሥታት እጅ ወሰድን፤
9(ሲዶናውያን አርሞንዔምን ሢርዮን ብለው ይጠሩታል፥ አሞራውያንም ሳኔር ብለው ይጠሩታል) ፤
10በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ በባሳንም ያሉትን የዐግን መንግሥት ከተሞች እስከ ስልካና፤እስከ ኤድራይ ድረስ ባሳንን ሁሉ ወሰድን።
11ከራፋይም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን ተርፎ ነበር፤ እነሆም አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በረባት አልኖረምን? ይህም በሰው ክንድ ልክ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ነበረ።
12በዚያን ጊዜ በአርሞን ሸለቆ ከአሮዔር ርስት አድርገን የወሰደነውን ይህን የገለዓድን ተራራማ ምድር እኩልታ ከተሞቹንም ለሮቤልና ለጋድ ነገድ ሰጠኋቸው።
13ከገለዓድም የቀረውን የዐግንም መንግሥት ባሳንን ሁሉ የአጎብንም ምድር ሁሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ። (ይህም ተመሳሳይ አገር የራፋይም ምድር ተብሎ ይቆጠራል።)
14የምናሴ ነገድ አንዱ ኢያዕር እስከ ሄሸራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ ድረስ የአርጎብን አካባቢ ሁሉ ወሰደ። ይህንም የባሳንን ምድር እስከ ዛሬ ድረስ የሚጠራውን በስሙ የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራ።
15ለማኪርም ገለዓድን ሰጠሁት።
16ለሮቤል ነገድና ለጋድም ነገድ ከገለዓድ ጀምሮ እስከ አርግኖን ሸለቆ ድረስ የሸለቆውን እኩሌታ ዳርቻውንም እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ ሰጠኋቸው።
17ከኪኔሬት እስከ ዓርባ ባሕር (እርሱም የጨው ባሕር) ድረስ ከፈስጋ ተራራ በታች ወደ ምሥራቅ ያለውን የዮርዳኖስን ሸለቆ ዳቻውንም ሰጠኋቸው።
18በዚያም ጊዜ እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፦ እግዚአብሔር አምላካችሁ ይህን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ እናንተ የጦር ሰዎች መሣሪያችሁን ታጥቃችሁ በወንድሞቻችሁ ከእስራኤል ልጆች ፊት ታልፋላችሁ።
19ነገር ግን ሚስቶቻችሁ፥ ልጆቻችሁና ከብቶቻችሁ (ብዙ ከብቶች እንዳሉአችሁ አውቃለሁ) በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤
20ይኸውም እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፈም ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ እግዚአብሔር አምላካችሁ የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።
21በዚያም ጊዜ ኢያሱን እንዲህ ብዬ አዘዝሁት፦አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥታት ያደረገውን ሁሉ ዓይኖችህ አይተዋል፤ እንዲሁ በምታልፍባቸው መንግሥታትም ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያደርጋል።
22አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ ስለ እናንት ስለሚዋጋ አትፈራቸውም ብዬ አዘዝሁት።
23በዚያም ጊዜ እኔ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ለመንሁ፦
24ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ታላቅነትህንና ብርቱ እጅህን ለእኔ ለባሪያህ ማሳየት ጀምረሃል፤ በሰማይ ወይም በምድር እንደ አንተ፥ እንደ ኃይልህ፥ ያደርግ ዘንድ የሚችል አምላክ ማን ነው?
25እኔም ወደዚያ ልሂድና በዮርዳኖስም ማዶ ያለውን መልካሙን ምድርና መልካሙን ተራራማውን አገር ሊባኖስንም ለመየት እለምንሃለሁ።
26እግዚአብሔር ግን እናንተ ባለመስማታችሁ ምክንያት ተቆጣኝ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ስለዚህም ነገር ደግመህ እንዳትናገረኝ ይበቃሃል።
27ይህን ዮርዳኖስን ስለማትሻገር ወደ ፈስጋ ራስ ውጣና ዓይንህንም ወደ ምዕራብ፥ ወደ ሰሜን፥ ወደ ደቡብምና ወደ ምሥራቅ ዓይንህን አንሥተህ ተመልከት።
28በዚህ ፈንታ ኢያሱን አስተምራው፥ አደፋፍረው እንዲሁም አጽናው፤ ምክንያቱም እርሱ በዚህ ሕዝብ ፊት ይሄዳል፥ አንተም የምታየውን ምድር ያወርሳቸዋል።
29ስለዚህም በቤተ ፌጎርም በሸለቆው ውስጥ ቆየን።