መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

አሞጽ 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፥ እንዲህም አለ፦«መሠረቶቹ እንዲናወጡ የአምዶቹን የላይኛውን ጫፍ ምታ። በራሶቻቸው ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፥ ከእነርሱም የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ። ከእነርሱ ማንም አያመልጥም፥ ማንም አይተርፍም።
2ቆፍረው ወደ ሲዖል ቢወርዱም፥ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች። ወደ ሰማይ ቢወጡም፥ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ።
3በቀርሜሎስ ራስ ላይ ቢሸሸጉም፥ በርብሬ ከዚያ እወስዳቸዋለሁ። በባሕሩ ሥር ከዓይኔ ቢደበቁም፥ በዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል።
4በጠላቶቻቸው ፊት እየተነዱ ወደ ምርኮ ይጋዛሉ፤ በዚያም ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል። ዓይኔን ለክፉ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፥ ለመልካምም አይደለም።»
5ጌታ፥ የሠራዊቱ እግዚአብሔር ምድርን ይዳስሳል፥ እርስዋም ትቀልጣለች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሁሉ፤ ሁለመናዋ እንደ ወንዝ ወደ ላይ ይወረወራል፥ እንደ ግብጽም ወንዝ ተመልሶ ይሰምጣል።
6አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ግምጃ ቤቱን በምድር የመሠረተ እርሱ ነው። የባሕርን ዉኆች ይጠራቸዋል፥ በምድርም ፊት ላይ ያፈስሳቸዋል፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው።
7የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ፥ፍልስጤማያንን ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?
8እነሆ፥ የጌታ እግዚአብሔር ዓይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ገጽ አጠፋዋለሁ፣ የያቆብን ቤት ግን ፈጽሜ አላጠፋም፤ ይላል እግዚአብሔር።»
9እነሆ፥አዝዛለሁ፥ ሰው በወንፊት እህል እንደሚነፋ፥ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እነፋለሁ፤ ነገር ግን አንዲትም ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።
10«ጥፋት አይደርስብንም ወይም አያገኘንም» የሚሉ፤ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ።
11«በዚያን ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሳለሁ፥ ሽንቁሩንም እዘጋለሁ። ፍራሽዋንም አነሳለሁ፥ በቀድሞ ዘመን እንደነበረች እን ደገና እሠራታለሁ፤
12ይኼውም የኤዶምን ቅሬታ፥ በስሜም የተጠሩትን አሕዛብ ሁሉ ይወርሱ ዘንድ ነው፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።»
13እነሆ፥ አራሹ አጫጁ ላይ፥ ወይን ጠማቂው ዘሪው ላይ የሚደርስበት ጊዜ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። ተራሮቹ ጣፋጩን ወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይፈስባቸዋል።
14ሕዝቤን እስራኤልን ከተማረከበት እመልሰዋለሁ። የፈረሱትን ከተሞች ሠርተው ይኖሩባቸዋል፥ ወይንንም ተከለው የወይን ጠጃቸውን ይጠጣሉ፥አትክልትም ተክለው ፍርውን ይበላሉ።
15በምድራቸው ላይ እተክላቸዋለሁ፥ ከሰጠኋቸውም ምድር ከቶውን ዳግመኛ አይነቀሉም» ይላል አምላካችሁ እግዚአብሔር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።