መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

2ኛ ተሰሎንቄ 3

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፣ በእናንተ ዘንድ ደግሞ እንደሚሆነው የጌታ ቃል በፍጥነት እንዲዳረስና እንዲከበር ስለ እኛ ጸልዩ፣
2ሁሉ እምነት ያላቸው አይደሉምና ከአመጸኞችና ከክፉዎች ሰዎች እንድንድን ጸልዩልን።
3ነገር ግን የሚያጸናችሁና ከክፉው የሚጠብቃችሁ ጌታ የታመነ ነው።
4ያዘዝናችሁን ነገሮች እንደጠበቃችሁና ወደፊትም እንደምትጠብቁ ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል።
5ጌታ ልባችሁን ወደ እግዚአብሔር ፍቅርና ወደ ክርስቶስ ጽናት ይምራው።
6ወንድሞች ሆይ፣ ከእኛ እንደተቀበላችሁት ልማድ ሳይሆን ሥራ በመፍታት ከሚኖር ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።
7እንዴት ምሳሌነታችንን መከተል እንደሚኖርባችሁ እናንተው ታውቃላችሁ። በመካከላችሁ በስንፍና አልተመላለስንም፣
8ወይም ገንዘብ ሳንከፍል የማንንም ምግብ አልበላንም። ከዚያ ይልቅ ከእናንተ በማንም ላይ ሸክም ላለመሆን በድካምና በጥረት ሌሊትና ቀን ሠራን።
9ይህንን ያደረግነው እኛን ትመስሉ ዘንድ ምሳሌ ልንሆንላችሁ ብለን እንጂ ሥልጣን ስላልነበረን አይደለም።
10ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ “ሊሠራ የማይወድ ማንም ቢኖር እርሱ መብላት የለበትም” ብለን አዝዘናችሁ ነበር።
11በመካከላችሁ ሥራ ፈት ሆነው የሚመላለሱ አንዳንዶች መኖራቸውን ሰምተናልና፤ ሥራ አይሠሩም ነገር ግን በሰው ጉዳይ ጣልቃ ይገባሉ።
12እንደነዚህ ያሉትን በጸጥታ እንዲሠሩና የራሳቸውን ምግብ እንዲበሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸዋለንም።
13እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ፣ ትክክል የሆነውን ከማድረግ አትታክቱ፡፡
14በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ያለውን ቃላችንን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር ይህንን ሰው ልብ በሉት፣ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር ኅብረት አታድርጉ፡፡
15እንደ ወንድም ገስጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቁጠሩት፡፡
16የሰላም ጌታ ራሱ ሁልጊዜ በሁሉ መንገድ ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
17እኔ ጳውሎስ፣ ሰላምታዬ እንዲህ ነው፣ በራሴ እጅ በምጽፋቸው ደብዳቤዎች ሁሉ ላይ ምልክቴ ይህ ነው።
18የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።