1እንግዲህ እኔም ከእነርሱ ጋር ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤
2ስለዚህ፣ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቋቸውም ማድረግ ስላለባችሁ በግዴታ ሳይሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በደስታ ይሁን፤ ጥቅም ለማግኘት በመስገብገብ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃደኝነት ይሁን፤
3እንዲሁም በእናንተ ኀላፊነት ሥር ላለው መንጋ መልካም ምሳሌ ሁኑ እንጂ እንደ ዐለቃ በላያቸው አትሠልጥኑ።
4የእረኞች ዐለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።
5ጕልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን ለብሳችሁ አንዱ ሌላውን ያገልግል፤ ምክንያቱም፣ «እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል» እንደ ተባለው፣
6እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤
7እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
8ጠንቃቆች ሁኑ፤ ንቁም፤ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል።
9በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
10ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ ፣ በክርስቶስ ወደ ዘለዓለማዊ ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል ፤ ያበረታችኋልም።
11የገዥነት ሥልጣን ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን! አሜን።
12እንደ ታማኝ ወንድም በምቈጥረው በስልዋኖስ አማካይነት ይህን ዐጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍሁላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልመሰክርላችሁ ነው። በዚህ ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ።
13ከእናንተ ጋር የተመረጠችው፣ በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ እንዲሁም ልጄ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል።
14በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁም ሰላም ይሁን።