1ስለክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆነው ጳውሎስ ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ ጋር ለተወደደው ወንድማችንና የሥራ አጋራችን ለሆነው ለፊሊሞና፣
2ለእህታችን ለአፒፊያ፣አብሮን ወታደር ለሆነው ለአክሪፋ እንዲሁም በቤትህ ላለችው ቤተክርስቲያን፡
3ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሠላም ለእናንተ ይሁን።
4በጸሎቴ ሁሉ ስላንተ እያነሳሁ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
5ምክንያቱም በጌታ በኢየሱስ ስላለህ እምነት ለቅዱሳንም ሁሉ ስላለህ ፍቅር ሰምቻለሁ።
6በክርስቶስ በኩል የመልካም ነገር ሁሉ እውቀት በእኛ ውስጥ ስላለ በእምነት ያለህ ተካፋይነት ውጤታማ እንዲሆን እጸልያለሁ።
7ወንድሜ ሆይ፣ ለዚህም ምክንያቱ የቅዱሳን ሁሉ ልብ በአንተ በማረፉ ምክንያት በፍቅርህ በጣም ደስ ስላለኝና ስለተጽናናሁ ነው።
8ስለዚህም ምንም እንኳ ምን ማድረግ እንዳለብህ በክርስቶስ ለማዘዝ ድፍረት ቢኖረኝም
9በዚህ ፈንታ እንደ ሽማግሌው አሁን ደግሞ ስለ ክርስቶስ እስረኛ እንደሆነው ጳውሎስ በፍቅር እለምንሀለሁ።
10ልመናዬ በእስርቤት አባት ስለሆንኩት ስለ ልጄ ኦኖሲሞስ ነው።
11ምክንያቱም ቀድሞ ለአንተ የማይጠቅም አሁን ግን ለአንተም ለእኔም ጠቃሚ በመሆኑ ነው።
12የልቤ የሆነውን እርሱን ወደ አንተ ልኬዋለሁ።
13በእኔ በኩልስ አንተን ወክሎ ስለ ወንጌል በእስር ቤት ያለሁትን ያገለግለኝ ዘንድ እኔ ጋ ቢቀር እወድ ነበር።
14ነገር ግን መልካም ሥራህ በግድ ሳይሆን በፈቃድህ ይሆን ዘንድ ያለ አንተ ፈቃድ ምንም ማድረግ አልፈለግሁም።
15ለጥቂት ጊዜ ከአንተ ተለይቶ የነበረው ምናልባት ለዘላለም የአንተ ይሆን ዘንድ ነው ።
16ነገር ግን ከዚህ በኋላ ከባሪያ የተሻለ እንደተወደደ ወንድም እንጂ እንደባሪያ አይደለም፥ በተለይ ለእኔ የተወደደ ከሆነ ለአንተማ በሥጋም በጌታም የበለጠ ይሆናል።
17እንግዲህ እንደ አጋርህ ከቆጠርከኝ እንደኔ አድርገህ ተቀበለው።
18ነገር ግን በምንም መልኩ አሳዝኖህ ቢሆን ወይም ዕዳ ቢኖርበት በእኔ ላይ ቁጠረው።
19እኔ ጳውሎስ እኔ እከፍላለሁ ብዬ በገዛ እጄ ጽፌአለሁ።የገዛ ህይወትህ እንኳ የኔ ነው ብዬህ አላውቅም።
20አዎ ወንድሜ ሆይ እስኪ በጌታ ደስ ይበለኝ፥ ልቤም በክርስቶስ ይጽናና።
21እንደምትታዘዘኝ በመተማመን ካልኩህም በላይ እንደምታደርግ ስለማውቅ ጽፌልሀለሁ።
22በነገራችን ላይ ከጸሎታችሁ የተነሳ ወደ እናንተ እንደምመጣ ተስፋ ስለማደርግ አንድ የእንግዳ ክፍል አዘጋጅልኝ።
23ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አብሮኝ የታሰረው ኤጳፍራ
24እንዲሁም የሥራ አጋሮቼ ማርቆስ፣አርስጥሮኮስ፣ዴማስና ሉቃስ ሠላምታ ያቀርቡልሀል።
25የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን!