1የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶም እንዲህ ይላል፦ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት ሰምተናል፥ መልእክተኛውም በአሕዛብ መካከል ተልኮ፥«ተነሡ! እርሷን ለመውጋት እንነሣ» ብሎአል።
2አነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ታናሽ አደርግሃለሁ፥እጅግ የተናቅህ ትሆናለህ።
3አንተ በዓለት ስንጣቂ ውስጥ፥በከፍታ ሥፍራ በሚገኝ ቤት የምትኖር፥ በልብህም «ማን ወደ ምድር ያወርደኛል?» የምትል ሆይ፥የልብህ ኩራት አታልሎሃል።
4እንደ ንስር እጅግ ከፍ ከፍ ብትል እንኳ፥ጎጆህም በከዋክብት መካከል ቢሆን እንኳ፥እኔ ከዚያ አወርድሃለሁ ይላል እግዚአብ ሔር።
5ሌቦች ወደ አንተ ቢመጡ፥ዘራፊዎች በሌሊት ቢመጡ (አንተ እንዴት ተቆረጥህ!) ፥የሚበቃቸውን ያህል ብቻ የሚሰርቁ አይደለምን? ወይን ለቃሚዎች ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ አያስቀሩምን?
6ዔሳው ምንኛ ተበረበረ፥የተደበቀ ሀብቱ ምንኛ ተዘረፈ?
7የተማማልሃቸው ሰዎች፥በጉዞህ ወደ ድንበር ይሰድዱሃል።ከአንተ ጋር መልካም ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች አታለሉህ፥አሸነፉህም። እንጀራህን የበሉ ከበታችህ ወጥመድ ዘረጉብህ። በእርሱም ዘንድ ማስተዋል የለም።
8በዚያ ቀን ከኤዶም ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል እግዚአብሔር።
9ቴማን ሆይ፥ ሰው ሁሉ ከዔሳው ተራራ ታርዶ ይጠፋ ዘንድ፤፡ኃያላንህ ይደነግጣሉ።
10በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተፈጸመ ግፍ፥እፍረት ይከድንሃል፥ለዘላለምም ትጠፋለህ።
11እንግዶች ሀብቱን በዘረፉበት፥ባዕዳንም በበሮቹ በገቡበት፥በኢየሩሳሌምም ላይ ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን፤አንተም ገለልተኛ ሆነህ በቆምህበት ቀን፥ ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆነሃል።
12ነገር ግን ወንድምህ በገጠመው ክፉ ቀን ሐሴት ማድረግ አይገባህም ነበር፥በጥፋታቸው ቀን በይሁዳ ሕዝብ ላይ መደሰት አይገ ባህም ነበር፤በጭንቀታቸው ቀን ትኩራራ ዘንድ አይገባህም ነበር።
13በጥፋታቸው ቀን በሕዝቤ በር ትገባ ዘንድ አይገባህም ነበር፥በጥፋታቸው ቀን በመ ከራቸው ሐሴት ማድረግ አይገባህም ነበር፤በጥፋታቸው ቀን ሀብታቸውን መዝረፍ አይገባህም ነበር።
14የሸሹትን ለመግደል በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትቆም ዘንድ አይገባህም ነበር፤በጭንቀት ቀን የተረፉለትን አሳልፈህ መስጠት አይገባህም ነበር።
15የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና። እንዳደረግኽው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ሥራህ በገዛ ራስህ ላይ ይመለሳል።
16በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደጠጣችሁ፥ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ። ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፤ ከዚህ በፊት እንዳልሆኑት ይሆናሉ።
17በጽዮን ተራራ ያመለጡ ይገኛሉ፥ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፤ የያዕቆብም ቤት የገዛ ራሱን ርስት ይወርሳል።
18የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባል፥ የዔሳውም ቤት ገለባ ይሆናሉ፤ያቃጥሉታል፥ይበሉታልም። ከኤሳው ቤት የሚተርፍ አይኖርም፥እግዚአብሔር ተናግሮአልና።
19የኔጌብ ሰዎች የዔሳውን ተራራ ይወርሳሉ፥የቆላውም ሰዎች፦የፍልስጥኤማውያንን ምድር፥የኤፍሬምን ምድር፥ የሰማሪያንም ምድር ይወርሳሉ፤ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል።
20የእስራኤል ሕዝብ ሠራዊት ምርኮኞች የከንዓንን ምድር እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳሉ። በስፋራድም የሚኖሩ የእስራኤል ምርኮኞች የኔጌብን ከተሞች ይወርሳሉ።
21በዔሳው ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ ነጻ አውጪዎች ወድ ጽዮን ተራራ ይወጣሉ፤ መንግሥቱም የእግዚአብሔር ይሆናል።