መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ይሁዳ 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ፥ የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፤ ለተጠሩት፥ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቁት፤
2ምሕረት ለእናንተ ይሁን፤ ሰላምና ፍቅርም ይብዛላችሁ።
3ወዳጆች ሆይ፤ አብረን ስለምንካፈለው ድነት ልጽፍላችሁ ጥረት እያደረግሁ ሳለ፥ ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለተሰጠው እምነት ጸንታችሁ ትጋደሉ ዘንድ ለመምከር እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።
4ለፍርድ እንደሚዳረጉ ከብዙ ዘመን በፊት የተጻፈባቸው አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና። እነዚህ ሰዎች ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው፥ የእግዚአብሔርን ጸጋ በሴሰኝነት የሚለውጡ፥ እርሱ ብቻ ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።
5ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ሁሉን የምታውቁት ቢሆንም ጌታ አንድ ጊዜ ሕዝቡን ከግብጽ አውጥቶ እንደ አዳናቸው በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋቸው ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።
6እንዲሁም የነበራቸውን የሥልጣን ደረጃ ባለመጠበቅ ተገቢ የመኖሪያ ስፍራቸውን የተውትን መላእክት እግዚአብሔር እስከ ታላቁ የፍርድ ቀን ድረስ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓል።
7እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩት ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ ራሳቸውን ለሴሰኝነትና ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ ለሆነ ግብረ ሥጋ ግንኙነት አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት ተጥለው ለሚሰቃዩት ምሳሌ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
8በዚህ ሁኔታ እነዚህ ደግሞ በሚያልሙት ሕልማቸው የራሳቸውን ሥጋ ያረክሳሉ፤ሥልጣንን ይቃወማሉ፤በሰማይ ክብር ያላቸውንም ይሳደባሉ።
9የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንኳ ዲያብሎስን በመቃወም ስለ ሙሴ ሥጋ በተከራከረው ጊዜ «ጌታ ይገሥጽህ» አለው እንጂ በእርሱ ላይ ሊፈርድ ወይም አንዳች የስድብ ቃል ሊናገር አልደፈረም።
10እነዚህ ሰዎች ግን የማያውቋቸውን ነገሮች ሁሉ ይሳደባሉ። እነርሱም አእምሮ የሌላቸው እንስሳት እንደሚያደርጉት በደመ ነፍስ በሚያውቋቸው ነገሮች ይጠፋሉ።
11ወዮላቸው፤ በቃየን መንገድ ሄደዋልና፤ለገንዘብ ሲሉ በበለዓም ስህተት ውስጥ ወድቀዋልና፤በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋልና።
12እነዚህ በፍቅር ግብዣችሁ ላይ አብረዋችሁ ሲጋበዙ ችግር የሚፈጥሩባችሁ ድብቅ እንቅፋቶች ናቸው፤ ደግሞም ያለ ሃፍረት ራሳቸውን ብቻ የሚመግቡ እረኞች ናቸው። እነርሱም በነፋስ የሚነዱ ውሃ አልባ ደመናዎች ናቸው፤ በመከር ወራት ፍሬ የማይገኝባቸው፥ ከሥራቸው የተነቀሉና ሁለት ጊዜ የሞቱ ዛፎች ናቸው።
13የራሳቸውን የነውር አረፋ የሚደፍቁ የተቆጣ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማም ለዘላለም የተጠበቀላቸው ተንከራታች ከዋክብት ናቸው።
14ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል፤ «እነሆ፤ ጌታ ከብዙ ሺህ ቅዱሳኑ ጋር ይመጣል።
15የሚመጣውም በሰው ሁሉ ላይ ለመፍረድ እንዲሁም ዐመፀኞችንና ኀጢአተኞችን ክፋት በተሞላበት ሁኔታ በፈጸሙት የዐመፅ ሥራቸውና በእግዚአብሔር ላይ በተናገሩት የስድብ ቃል ለመውቀስ ነው።»
16እነዚህ የሚያጉረመርሙ፥ ሌላውን የሚከሱ፥ የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ፥ ጉራ የሚነዙና ጥቅም ለማግኘትም ሰዎችን የሚክቡ ናቸው።
17እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን ቃል አስታውሱ
18ለእናንተም ሲናገሩ፥«በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ» ብለዋል።
19እነዚህ በሰዎች መካከል መለያየትን የሚፈጥሩ፥የሥጋን ምኞት የሚከተሉና መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ናቸው።
20እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ።
21በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ፤የዘላለም ሕይወትም ታገኙ ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ፈልጉ።
22ለሚጠራጠሩ ሰዎች ርኅራኄ አድርጉላቸው፤
23ከእሳት ነጥቃችሁ በማውጣት አንዳንዶችን አድኑ፤ ለሌሎች ድግሞ በእርኩስ ሥጋ የተበከለውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ምህረት አሳዩአቸው።
24እንግዲህ ከመውደቅ ሊጠብቃችሁ፥ ነቀፋ ሳይኖርባችሁ በታላቅ ደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችለው
25በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት አዳኛችን ለሆነው ብቸኛ አምላክ ከዘመናት ሁሉ በፊት፥ አሁንና እስከ ዘላለም ድረስ ክብር፥ ግርማ፥ ኀይልና ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።