መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 36

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንዲህም ሆነ፣ በንጉሡ ሕዝቅያስ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጥቶ ያዛቸው።
2ከዚያም፣ የአሦርም ንጉሥ ራፋስቂስን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፣ እርሱም በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኵሬ መስኖ አጠገብ ቆመ።
3የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ።
4ራፋስቂስም እንዲህ አላቸው፣ "ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፣ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፣ "ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው?
5እኔ፣ ለሰልፍ የሆነው ምክርህና ኃያልህ ከንቱ ነገር ነው አልሁ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?
6ተመልከት፣ እየታመንክ ያለኸው በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ነው። ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል። የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ አንዲሁ ነው።
7አንተም፣ "በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፣ "በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ" ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ይስፈረሰ ይህ አይደለምን?
8አሁን እንግዲህ፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር በመልካም ተደራደር። የሚጋልቡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።
9ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሶኞች በግብጽ ስትታመን፣ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል?
10አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን አገር አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር፣ "ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው" አለኝ።
11ከዚያም ኤልያቄምና ሳምናስ፣ ዮአስም ራፋስቂስን፣ "እኛ እንሰማለንና እባክህ፣ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን" አሉት።
12ራፋስቂስ ግን፣ "ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ዐይነምድራቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን?" አላቸው።
13ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፣ "የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ፤
14ንጉሡ እንዲህ ይላል፣ 'ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ።
15ሕዝቅያስም፣ "እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም" ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።
16ሕዝቅያስንም አትስሙ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፦ 'ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ። እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፣ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ።
17ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፣ እህልና የወይን ጠጅ፣ እንጀራና ወይን ወዳለበት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው።'
18ሕዝቅያስም፣ 'እግዚአብሔር ያድነናል' ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን?
19የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?
20እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?"
21ነገር ግን ንጉሡ አንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና ሕዝቡ ዝም አሉ፣ አንዳችም አልመለሱለትም።
22ከዚያም የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፣ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።