1በአንጾኪያም ባለችው ጉባኤ አንዳንድ ነቢያትና መምህራን ነበሩ። እነርሱም በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ወንድሙ ምናሔ፣ ሳውልም ነበሩ።
2ጌታን እያመለኩና እየጾሙ እያሉ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ “ለጠራኋቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ” አለ።
3ጉባኤው ከጾመ፣ ከጸለየና እጅ ከጫነም በኋላ አሰናበታቸው።
4በርናባስና ሳውልም ለመንፈስ ቅዱስ ታዘዙና ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ሄዱ።
5በስልማና ከተማ በነበሩ ጊዜም፣ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ። ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ሊረዳቸው አብሯቸው ነበር።
6በደሴቲቱም ሁሉ እስከ ጳፉ በሄዱ ጊዜ፣ ስሙ በርያሱስ የተባለ፣ አንድ አይሁዳዊ የሐሰት ነቢይና አስማተኛ አገኙ።
7ይህ አስማተኛ አስተዋይ ሰው ከነበረው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አገረ ገዥ ጋር ተባበረ። ይህ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ስለ ፈለገ፣ በርናባስናን ሳውልን ጠራ።
8ነገር ግን፣ “አስማተኛው” ኤልማስ ስሙ ሲተረጎም እንዲሁ ነውና ተቃወማቸው፤ አገረ ገዡን ከእምነቱ ለመመለስ ሞከረ።
9ደግሞ ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ፤ ትኵር ብሎም ተመለከተውና
10እንዲህ አለው፤ “አንተ የዲያብሎስ ልጅ፣ ክፋትና ተንኮል ሁሉ የሞላብህ ነህ። የጽድቅ ሁሉ ጠላት ነህ። የቀናችውን የጌታን መንገድ ማጣመምህን አታቆምምን?
11አሁንም ተመልከት፤ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ነችና ትታወራለህ። ለጥቂት ጊዜ ፀሐይን አታይም።” ወዲያውኑ በኤልማስ ጨለማና ጭጋግ ወደቀበት፤ እጁንም ይዘው እንዲመሩት ሰዎችን እየጠየቀ ይዘዋወር ጀመር።
12አገረ ገዡ የሆነውን ካየ በኋላ፣ ስለ ኢየሱስ በቀረበው ትምህርት ስለ ተደነቀ፣ አመነ።
13ጳውሎስና ጓደኞቹም በመርከብ ከጳፉ ተነሥተው በጵንፍልያ ወዳለችው ወደ ጴርጌን መጡ። ዮሐንስ ግን ትቶአቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
14ጳውሎስና ጓደኞቹ ከጴርጌን ተጕዘው የጲስድያ ወደ ሆነችው አንጾኪያ መጡ። በዚያ በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ።
15ሕግና ነቢያት ከተነበቡ በኋላ፣ የምኵራብ አለቆች፣ “ወንድሞች ሆይ፣ እዚህ ላሉት ሕዝብ የሚሆን የሚያበረታታ መልእክት ካላችሁ፣ ተናገሩ” በማለት መልእክት ላኩላቸው።
16ጳውሎስም ቆመና በእጁ ምልክት ሰጥቶ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎችና እናንተ እግዚአብሔርን የምታከብሩ፣ ስሙ።
17የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ ይኖሩ በነበሩበት ጊዜ፣ ሕዝቡን አበዛላቸው፤ በተዘረጋችም ክንድ መርቶ ከዚያ አወጣቸው።
18ለአርባ ዓመታት ገደማ በምድረ በዳ ታገሣቸው።
19በከነዓን ምድርም ሰባት ሕዝቦችን ካጠፋ በኋላ፣ ምድራቸውን ለሕዝባችን ርስት አድርጎ ሰጠ።
20እነዚህ ሁነቶች ሁሉ በአራት መቶ ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ተፈጸሙ። ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በኋላ፣ እግዚአብሔር እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው።
21ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡ ንጉሥ ይንገሥልን ብለው ጠየቁ፤ ስለሆነም፣ እግዚአብሔር ከብንያም ነገድ የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመታት ሰጣቸው።
22ከዚያም እግዚአብሔር እርሱን ከንጉሥነት ከሻረው በኋላ፣ ንጉሣቸው እንዲሆን ዳዊትን አስነሣ። እግዚአብሔር፣ ‘እንደ ልቤ የሆነውን የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤ እርሱ እኔ የምፈልገውን ሁሉ ያደርጋል’ በማለት ስለ ዳዊት ተናግሮ ነበር።
23ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠ አዳኝ ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ።
24ይህ መሆን የጀመረው ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ መጀመሪያ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ባወጀ ጊዜ ነው።
25ዮሐንስ ሥራውን እንደ ጨረሰ እንዲህ አለ፤ ‘ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔ እርሱ አይደለሁም። ነገር ግን ስሙ፤ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ እርሱ ይመጣል።’
26ወንድሞች፣ የአብርሃም ዘር ልጆች፣ እግዚአብሔርንም የምታመልኩ ሆይ፣ የዚህ ድነት መልእክት የተላከው ለእኛ ነው።
27በኢየሩሳሌም የሚኖሩ፣ አለቆቻቸውም በእርግጥ ኢየሱስን አላወቁትም፤ በየሰንበቱ የሚነበበውን የነቢያትን ድምፅም በእውነት አልተረዱም፤ ስለ ሆነም በኢየሱስ ላይ ሞት በመፍረድ የነቢያትን ቃል ፈጸሙ።
28ምንም እንኳ በእርሱ ላይ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት ባያገኙም፣ እንዲገድለው ጲላጦስን ለመኑት።
29ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜም፣ ከዕንጨት ላይ አውርደው በመቃብር አኖሩት።
30እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው።
31ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም የወጡት ብዙዎች ለአያሌ ቀናት ዐዩት። እነዚህ ሰዎች አሁን ለሕዝቡ የሚናገሩ የእርሱ ምስክሮች ናቸው።
32ስለ ሆነም እኛ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ተስፋ የሚናገር የምሥራች እናመጣላችኋለን፤
33ኢየሱስን ከሙታን በማስነሣት እግዚአብሔር እነዚህን ተስፋዎች ለእኛ ለልጆቻቸው ጠብቆአል። ይህም ደግሞ በሁለተኛው መዝሙር፦ ‘አንተ ልጄ ነህ፣ እኔ ዛሬ ወለድሁህ’ ተብሎ የተጻፈ ነው።’
34ደግሞም ሥጋው እንዳይበሰብስ ከሙታን እንዳስነሣው፦ ‘የተቀደሰውንና እውነተኛውን የዳዊት በረከት እሰጥሃለሁ’ ብሎ ተናግሯል።
35በሌላ መዝሙርም፣ ‘ቅዱስህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ የሚለው ስለዚህ ነው።
36ዳዊትም በዘመኑ የእግዚአብሔርን ዐሳብ አገልግሎ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ መበስበስንም ዐየ።
37እግዚአብሔር ያስነሣው ኢየሱስ ግን መበስበስን አላየም።
38ስለ ሆነም ወንድሞች ሆይ፣ በዚህ ሰው በኩል የኃጢአት ይቅርታ እንደ ተሰበከላችሁ ይህ ለእናንተ የታወቀ ይሁን።
39በሙሴም ሕግ እንድትጸድቁበት ከማይቻላችሁ ሁሉ፣ በእርሱ የሚያምን ሁሉ ጸድቆአል።
40እንግዲያው ነቢያት እንዲህ ሲሉ የተናገሩለት ነገር እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፦
41‘እናንተ የምትንቁ፣ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፣ ጥፉም፤ አንድ ስንኳ ቢነግራችሁ ከቶ የማታምኑትን ሥራ፣ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’”
42ጳውሎስና በርናባስ እንደ ወጡ፣ በሚቀጥለው ሰንበት ይህንኑ ቃል ደግመው እንዲናገሩ ሕዝቡ ለመኑአቸው።
43የምኵራቡ ስብሰባ እንዳበቃም፣ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ከገቡ ከሚያመልኩ ብዙዎቹ፣ በእግዚአብሔር ጸጋ እንዲጸኑ የመከሩአቸውን ጳውሎስና በርናባስን ተከተሉአቸው።
44በሚቀጥለውም ሰንበት፣ ጥቂቶች ሲቀሩ፣ መላው ከተማ የጌታን ቃል ለመስማት አንድ ላይ ተሰበሰበ።
45አይሁድ ሕዝቡን ባዩ ጊዜ፣ ቅንዓት ሞላባቸውና ጳውሎስ የተናገረውን ተቃወሙ፣ ሰደቡትም።
46ጳውሎስና በርናባስ በድፍረት ተናገሩ፤ እንዲህም አሉ፤ “የእግዚአብሔር ቃል መጀመሪያ ለእናንተ መነገሩ አስፈላጊ ነበር። ቃሉን ከራሳችሁ ስትገፉትና ለዘላለም ሕይወት የተገባችሁ እንዳልሆናችሁ ራሳችሁን ስትቈጥሩ ዐይተናችሁ፣ ወደ አሕዛብ ዘወር የምንል መሆናችንን ተመልከቱ።
47ጌታ፣ ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለድነት ትሆን ዘንድ፣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’” በማለት አዞናልና።
48አሕዛብ ይህን እንደ ሰሙ ደስ አላቸው። የጌታንም ቃል አከበሩ። ለዘላለም ሕይወት የተመረጡትም አመኑ።
49የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ።
50አይሁድ ግን የሚያመልኩትን ታዋቂ ሴቶችን፣ የከተማይቱን ታላላቅ ወንዶችንም ቀሰቀሱ። በጳውሎስና በበርናባስ ላይም ስደት አስነሥተው ከከተማቸው ዳርቻ ወዲያ አውጥተው ጣሏቸው።
51ጳውሎስና በርናባስ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራገፉባቸው። ከዚያም ወደ ኢቆንዮን ከተማ ሄዱ።
52ደቀ መዛሙርቱም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ነበር።